Jeremiah 27

የይሁዳ በናቡከደነፆር ሥር መውደቅ

1በይሁዳ ንጉሥ፣ በኢዮስያስ ልጅ በሴዴቅያስ
ጥቂት የዕብራይስጥ ጽሑፎችና የሱርሰት ትርጕም (ኤር 27፥312 እና 28፥1 ይመ)፣ አንዳንድ የዕብራይስጥ ጽሑፎች ኢዮአቄም ይላሉ (አብዛኛዎቹ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ይህ ጥቅስ ቍጥር የላቸውም)።
ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ላይ ይህ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ፤
2እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “የዕንጨት ቀንበር ሠርተህ በጠፍር ማነቆ አያይዘውና በዐንገትህ አስገባው፤ 3ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሴዴቅያስ፣ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት ሰዎች በኩል ለኤዶም፣ ለሞዓብ፣ ለአሞን፣ ለጢሮስና ለሲዶና ነገሥታት መልእክት ላክ። 4ለጌቶቻቸውም እንዲያሳውቁ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ለጌቶቻችሁ ይህን ንገሯቸው፤ 5በታላቁ ኀይሌና በተዘረጋው ክንዴ ምድርን፣ በላይዋ የሚኖሩትን ሰዎችና እንስሳት ፈጥሬአለሁ፤ ለምወድደውም እሰጣለሁ። 6አሁንም እነዚህን አገሮች ሁሉ ለአገልጋዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣለሁ፤ የዱር አራዊት እንኳ እንዲገዙለት አደርጋለሁ። 7የእርሱ አገር በተራው ለሌሎች እስከሚገዛበት ጊዜ ድረስ፣ ሕዝቦች ሁሉ ለእርሱ፣ ለልጁና ለልጅ ልጁ ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜ ብዙ ሕዝቦችና ታላላቅ ነገሥታት እርሱን ይገዙታል።

8“ ‘ “ነገር ግን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር የማይገዛ፣ ዐንገቱንም ከቀንበሩ በታች ዝቅ የማያደርግ ማንኛውንም ሕዝብ ወይም መንግሥት በእጁ እስከማጠፋው ድረስ በሰይፍና በራብ፣ በመቅሠፍትም እቀጣዋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር 9ስለዚህ፣ ‘የባቢሎንን ንጉሥ አታገለግሉም’ የሚሏችሁን ነቢያታችሁን፣ ሟርተኞቻችሁን፣ ሕልመኞቻችሁን፤ መናፍስት ጠሪዎቻችሁንና መተተኞቻቸሁን አትስሙ፤ 10ከምድራችሁ እንድትፈናቀሉ፣ እኔም እንዳሳድዳችሁና እንዳጠፋችሁ የሐሰት ትንቢት ይነግሯችኋልና። 11ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች ዐንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚያገለግለውን ማንኛውንም ሕዝብ በገዛ ምድሩ እንዲቀርና እያረሰም በዚያ እንዲኖር አደርገዋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።” ’ ”

12ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስም ይህንኑ መልእክት እንዲህ ብዬ ነገርሁት፤ “ዐንገታችሁን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች ዝቅ አድርጉ፤ እርሱንና ሕዝቡን አገልግሉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ። 13አንተና ሕዝብህ፣ እግዚአብሔር ለባቢሎን ንጉሥ አልገዛም ያለውን ሕዝብ ባስጠነቀቀበት በሰይፍ፣ በራብና በመቅሠፍት ለምን ታልቃላችሁ? 14ሐሰተኛ ትንቢት ስለሚነግሯችሁ፣ ‘የባቢሎንን ንጉሥ አታገለግሉም’ የሚሏችሁን ነቢያት አትስሙ፤ 15‘እኔ አልላክኋቸውም’ ይላል እግዚአብሔር ‘የሐሰት ትንቢት በስሜ ይናገራሉ፤ ስለዚህ እናንተንና ትንቢት የሚናገሩላችሁን ነቢያት አሳድዳለሁ፤ እናንተም ትጠፋላችሁ።’ ”

16እኔም ለካህናቱና ለዚህ ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አልሁ፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የእግዚአብሔር ቤት ዕቃ ከባቢሎን ቶሎ ይመለሳል’ የሚሏችሁን ነቢያት አትስሟቸው፤ የሚነግሯችሁ የሐሰት ትንቢት ነውና። 17ስለዚህ እነርሱን መስማት ትታችሁ ለባቢሎን ንጉሥ ተገዙ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ ባለመታዘዛችሁስ ይህች ከተማ ለምን ትፈራርስ? 18እውነተኞች ነቢያት ከሆኑና በርግጥ የእግዚአብሔር ቃል ካላቸው፣ በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት በኢየሩሳሌምም የቀሩት ዕቃዎች ወደ ባቢሎን እንዳይወሰዱ ወደ ሰራዊት ጌታ ወደ እግዚአብሔር እስቲ ይማልዱ! 19የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በዚህች ከተማ ስለ ቀሩት ዐምዶች፣ ከናስ ስለ ተሠራው ትልቁ ገንዳ፣ ስለ ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎችና ስለ ሌሎቹም ዕቃዎች እንዲህ ይላልና፤ 20የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን፣
ኢኮንያን የኢዮአኪን ሌላው አቻ ስም ነው።
ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ መኳንንት ጋር ማርኮ ወደ ባቢሎን በወሰደ ጊዜ እነዚህ በከተማዪቱ የቀሩ ዕቃዎች ስለሆኑ፣
21በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት በኢየሩሳሌምም ስለ ቀሩት ዕቃዎች፣ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ 22‘ወደ ባቢሎን ይወሰዳሉ፤ እስከምጐበኛቸውም ቀን ድረስ በዚያ ይቀመጣሉ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘በዚያ ጊዜም እመልሳቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ አመጣቸዋለሁ።’ ”

Copyright information for AmhNASV